የዘጸአት አፖስቶሊክ ሪፎርሜሽን ቤተክርስትያን አጭር ታሪክ

የቤተክርስቲያኒቱ ታሪክ ቤተክርስቲያኒቱን ከተከላት ከሐዋርያ ዮሀንስ ግርማ በእግዚአብሄር መነካትና ጥሪ ጋር በእጅጉ የተያያዘ ነው። በሚያዝያ ወር 1986 ዓ.ም በእግዚአብሄር ጉብኝት ህይወቱ የተለወጠው ሐዋርያ ዮሐንስ ከእግዚአብሄር በወቅቱ ከተቀበለው ትውልድን የማስነሳት ጥሪ የተነሳ ራሱን ለአገልግሎት ማዘጋጀት ይጀምራል። ለዚህም በወንጌል ስራ ላይ በመጠመድ እግዚአብሄር ብዙ ነፍሳትን ይሰጠዋል፤ እንዲሁም በወቅቱ በምድሪቱ ከነበረው የተሀድሶ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ እግዚአብሔር የአገልግሎትና ግንኙነት በሮችን ይከፍትለታል። በእነዚህ አገልግሎቶች እግዚአብሄር የሰጠውን ትውልድ ከሌሎች ወንድሞች ጋር እያገለገለ እርሱ ግን በዋናነት ለበለጠ አገልግሎት ራሱን ለማዘጋጀት ወደ ስነመለኮት ትምህርት ቤት በመግባት የመጀመሪያ ዲግሪውን በስነ-መለኮት ይማራል። ከዚህ በኋላ ራሱ ከጀመረውና ያገለግልበትም ከነበረው የተሐድሶ ህብረት መሪዎች ጋር በመነጋገርና በረከትን በመቀበል እግዚአብሔር የሰጠውን ራዕይ ለማገልገል ምሪትን ከእግዚአብሔር ተቀብሎ ተለይቶ ይወጣል። ከእርሱም ጋር ራሱ ወንጌል መስክሮ ደህንነት ካስተማራቸው ከመአዛ በፍቃዱ(ነብይት)፣አዲስ ተስፉ(መጋቢ)፣ብርቱካን ሀ/መስቀል(ወንጌላዊት)፣ዳንኤል ሀይሉ (መጋቢ)፣ ኤደን ሀይሉ (መጋቢ) እንዲሁም በሥጋ ወንድሙ ከሆነውና ከስሩ ተቀምጦ ለመገልገል ፈቃዱን ሰጥቶት ከተከተለው ጳውሎስ ግርማ ጋር ማገልገል ይጀምራሉ። ሐዋርያው ይታወቅበት ከነበረው የዝማሬ አምልኮ ጋር በተያያዘ አብረውት ከነበሩ አገልጋዮች ጋር የኳየር አገልግሎት በተለያዩ አቢያተ ክርስቲያናት በመስጠት እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚያገኛቸውን ወጣቶች ደቀመዝሙር በማድርግ አገልግሎቱ በመጀመሪያ በካፌዎች ከሚደረጉ የምክርና የህብረት ግዜያት እያደገ በመሄድ ለጥቂት ግዚያት በቅዱሳን መኖሪያ ቤት አገልግሎቱ የቀጠለ ሲሆን በኋላ ደግሞ በተለምዶ ጨርቆስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቤት በመከራየት አገልግሎቱን ይቀጥላል።

ከኳየር አገልግሎት በተጨማሪ የቤተክርስቲያኗን እድገትና ተጽዕኖ ካፋጠኑ ጉዳዮች መካከል የተማሪዎች አገልግሎት ተጠቃሹ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች አገልግሎት የብዙ ውጣቶች ህይወት መቀየር ምክንያት የሆኑና በተለይ በዳንዲቦሩ፣ በሴንት ጆሴፍ በኋላም በካቴደራል የነበሩ እንቅስቅሴዎች እንዲሁም ደግሞ የካምፓስ አገልግሎት መጀመር ለብዙ ወጣቶች ህይወት መቀየር ምክንያት ሆኗል።

የአገልግሎቱን መስፋት ተከትሎ ጨርቆስ አካባቢ ከነበረው ግቢ በተለምዶ ቡልጋርያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወደተገነባው ጊዜያዊ አዳራሽ በመዘዋወር አገልግሎቱን አጠናክሮ ይቀጥላል። በዚሁ ወቅት የቤ/ክ አገልግሎት የተጽዕኖ አድማሱን በማስፋትና ቤ/ክኒቱን በአለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ረገድ በአዲስ አበባ ኢግዚቢሽን ማዕከል የተደርጉት ትንቢታዊ የአምልኮ ጊዜያትና እነርሱን ተከትለው የተለቀቁት የኳየሩ የዲቪዲ አልበሞች እንዲሁም በአዲስ አበባ ስታዲየም ለሁለት ተከታታይ አመታት የተካሄዱ የጸሎትና ምልጃ ጊዚያት ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።

ሌላው በዚህ ወቅት ሃዋርያው የእ/ርን ምሪት በመከተል ስለጋብቻ በማስተማር እግዚአብሄር እንደተናገረው በጥቂት አመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በስሜት ሳይሆን በእውቀት ወደትዳር መግባታቸው ሌላው የቤተክርስቲያኒቱን እድገት ካፋጠኑ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ነው።

ከዚህ ባሻገር ቤተክርስቲያኒቱ በዚሁ ወቅት ሁለት አጥቢያዎችን አንዱን በመቀሌ (2001 ዓ.ም) ሌላውን በሆሳዕና (2002 ዓ.ም) ተክላ ወጣት ሚስዮናዊያን በመላክ ለብዙ ወጣቶች መዳን ምክንያት የሆኑ ተጽዕኖ ፈጣሪ አጥቢያዎች ለመሆን በቅተዋል::

የቤተክርስቲያኒቱ ፈጣን እድገት በፈጠረው አጣዳፊ የቦታ ችግር እንዲሁም ራዕዩን የሚመጥን ከባቢ በማስፈለጉ ቤተክርስቲያኒቱ ገቢ ወደ ማሰባሰብና ቦታ ወደማፈላለግ በመግባት በመጀመሪያ ቀን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀግብሯ ብቻ ታሪካዊ በሆነ ሁኔታ ከጥቂት ወጣት ምዕመናኗ ከ5 ሚልዮን ብር የሚበልጥ ገንዘብ መሰብሰብ ችላለች። ይህንን ተከትሎ ቦታ በማፍላልግ አሁን ቤተክርስቲያኒቱ የምትገኝበትን ሳርቤት ኦሮሚያ ቢሮዎች አጠገብ የሚገኘውን ቅጥር ግቢ መጀመሪያ በኪራይ ውል የተገኘ ቢሆንም እንገዛዋለን በሚል ጽኑ እምነት አሁን ያለውን አዳራሽ በምዕመናኑ ሁሉ አስደናቂ ተሳትፎ በአጭር ጊዜ ተገንብቶ ለአገልግሎት በቅቷል።

ቤተክርስቲያኒቱ ባደረገችው ተደጋጋሚ ገቢ ማሳባሰቢያዎች በተገኘ እንዲሁም ደግሞ ከብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ በተገኘ ብድር የማምለኪያ አዳራሽ የተገነባበት ቅጥር ግቢ ለመገዛት በቅቷል።ቤተክርስቲያኒቱ የባንኩን እዳ ሙሉ ለሙሉ በመክፈል በ2011 ዓ.ም አጠናቃ የማምለኪያ አዳራሹ ያረፈበትን ቦታ የራሷ አድርጋዋለች።

በአሁኑ ወቅት ቤተክርስቲያኒቱ በኢትዮጵያ ውስጥ 5 አጥቢያዎችና ከኢትዮጵያ ውጪ 3 ህብረቶች በስሯ ይገኛሉ።

ራዕይ

በዓለም ሁሉ ለጌታ የተገባ ትውልድ ተነስቶ ማየት

ተልእኮ

በዘመናችን በመጣልን እና ሊመጣ ባለው ሰማያዊ ጉብኝት ሁለንተናዊ የፅድቅ ተጽዕኖ በማምጣት የእግዚአብሔርን መንግስት ለማስፋት

ዋና እሴቶች

1
አምላካችን እግዚአብሔር ልዕለ ተፈጥሮአዊ ነው።
2
ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ነው።
3
እግዚአብሔራዊ ቤተሰብ የእግዚአብሔራዊ ትውልድ መሰረት ነው።
4
በእግዚአብሔር ለአላማ ተፈጥሬአለሁ።
5
ጊዜ በአላማ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ወድ ስጦታ ነው።

ይመዝገቡ

አዳዲስ መረጃዎች በፍጥነት እንዲደርስዎ የኢሜይል አድራሻዎትን እዚህ ጋር በማስገባት ይመዝገቡ